የካድሬው የፍቅር ደብዳቤ



ይድረስ ለምወድሽ ላፈቀርኩሽ ክብሬ። የጀመርነውን የፍቅርና የፎንቃ አቅጣጫን ለማስቀልበስ በመካከላችን ሰርገው የገቡትን የፍቅር ኪራይ ሰብሳቢዎች በጋራና በተናጥል በመሆን እንቅስቃሴያቸውን እንገታዋለን። የጀመርነውን የፍቅር ግስጋሴንም ለማስቀጠል አንድ ለአምስት በመሆን መቀጠል ባንችልም እኔና አንቺው ሆነን በ2025 መካከለኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ተርታ እንደምንመደብ ቃል እገባልሻለሁ። ውዴ..... ፍቅሬ..... እኔና አንቺ ከተገናኘን ጀምሮ የፍቅራችን ግለቱ ደብል ዲጂት መድረሱን መቼም ላንቺ መንገር አስፈላጊ አይመስለኝም። ውዴ... ፍቅራችንን ለማሳደግ የተጀመሩት የልማት እንቅስቃሴዎች አሁንም ይቀጥላሉ።
የውበት ድምቀትሽንም በማሳመር ከአፍሪካ ተወዳዳሪ የሆነች ተፈቃሪ አደርግሻለሁ። በየአቅጣጫው የተጀመሩት የፍቅር ርብርቦሻችንን በግንባር ቀድሞች ያላሰለሰ ጥረት እናሳካዋለን። የኔ ወድ.... አቤት የፍቅርሽ ግለቱ? ቀን እና ሌሊት ያለ እረፍት እየደከምኩ በአንድነትና በእኩልነት ላይ የተመሰረተውን ግንኙነታችንን አሁንም ለማስቀጠል ዘውትር እሰራለሁ። የአቀርቦት እጥረቶች በስግብግብ ግለሰቦች አማካኝነት ቢፈጠርም ስርአቱ በፈጠርው ምቹ የውድድር መድረክ ተጠቅሜ ጥቃቅን እና አነስተኛ የውበት እቃዎችን እያቀርብኩልሽ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሽ አደርግሻለሁ::
ያንቺው አፍቃሪ

Comments

Popular Posts