ሆያ ሆዬ በ ፒያሳ
የሐምሌ ወር ተገባዶ ነሐሴ ሲገባ ከዛሬ ሁለት አሥርት ዓመታት በፊት እኔና የሠፈር ጓደኞቼ በጉጉት የምንጠብቀው የቡሄ በዓል ሁሌም ትዝ ይለኛል።
ምንም እንኳን በዓሉን ለማክበር የእናቴ ተግሳጽ እና የፍልስለታ ፆም እንቅፋት ቢሆኑብኝም ያገኘኋትን ቀዳዳ በመጠቀም ባልተጻፈውና መንግሥት በማያውቀው የቀን መቁጠሪያችን የፀደቀውን የአምስት ቀናት የቡሄ በዓል ለማክበር የፒያሳን ሱቆች እናካልል ነበር፡፡
በዓሉ ለመድረስ 15 ወይም ከዚያ በላይ ቀናት ሲቀሩት እኔም ሆንኩ የዕድሜ እኩዮቼ ዜማችንን ለማድመቅ የምንጠቀምበትን «ኪሽኪሽ» ለመሥራት «በደቦ» ቆርኪ ለመልቀም በየመጠጥ ቤቱና በየቆሼው ስንርመጠመጥ እንከርማለን። መቼም አንባቢው እንደሚረዳው የቆሼው ትሩፋት ለጉንፋንና ለአልጋ የሚዳርገው ብዙዎቻችንን ነበር።
ቆርኪ ለቀማው ከተከናወነ በኋላ አቅማችን የፈቀደልንን ጉልበት በመጠቀም ቆርኪዋ ( እግረመንገዳችንን ጣታችንን) ቀጥቅጠን «ኪሽኪሽ» እናዘጋጃለን።
የፒያሳ ሆያ ሆዬ ከሌሎች አካባቢዎች ለየት የሚያደርጉት በርካታ ባህርያት ቢኖሩትም ትዝ የሚሉኝን ልጠቃቅስ።
በዓሉ ሊደርስ አንድ አምስት ቀናት ሲቀሩት ጭፈራችንን እንጀምራለን። የጭፈራችን ዋና ዓላማ ግን «ሽቀላ» ነው። በየሱቁ እየዞሩ ሳንቲም መልቀም ሰሞነኛ ሥራችን ይሆናል።
ለጭፈራው የምንመርጣቸው ቦታዎች ወርቅ ቤቶችን ሲሆን፤ መኪና ውስጥ የተቀመጡ ግለሰቦችንና በአካባቢ ለመገበያየት የመጡ የውጭ ሀገር ዜጐች ላይ እናተኩራለን፡፡ በአብዛኛው ግን ይህ ዕቅዳችን የሚሳካው በአካባቢ የፀጥታ አስከባሪዎች ወይም ደግሞ የሠፈሩ «ጉልቤዎች» ከሌሉ ነው።
«የፀጥታ አስከባሪዎችን ወይም ጉልቤዎችን መሸወድ ከቻልን ወርቅ ቤቶች በር ላይ ሆነን « ሆያ ሆዬ» ማለታችንን እንቀጥላለን። በየመሐሉ ግን ዓይናችንን የሳበችው ወርቅ ላይ ስናፈጥ ዜማው ግጥሙም ይጠፋና ጭፈራችንን ወደማቆም እንደርሳለን። በመሐል አንዱ ጐሸም ሲያደርገን «ሆ!» ማለት እንቀ ጥላለን።
በተመሳሳይ ሁኔታም መኪና ውስጥ ለተቀመጠ ሰው የመጨፈር ዕድል ከአገኘን ደመቅ አድርገን እንጨፍራለን። መኪናዋ ውስጥ የሚበላ ነገር ካየን የሁላችንም ዓይን እሷ ላይ ያፈጥና ምራቃችንን መዋጥ እንጀምራለን። አይ ልጅነት...!
በጭፈራ ወቅት የተገኘችውን ሳንቲም በዛ አድርጐ ለመካፈል እንዲመች የጨፋሪዎች ቁጥር ሦስት ቢበዛ ደግሞ አራት እንዲሆን ሕጋችን ያዛል። የተገኘውን ሳንቲም ደግሞ ከአካባቢው ጉልቤዎች ለማዳን በትንሿ ጭንቅላታችን መላ ያልነውን የተለያዩ ዘዴዎች እንጠ ቀማለን። በቀበቶ ማስገቢያ አካባቢ ያለውን የሱሪያችንን ክፍል በመቅደድ አሪፍ ቅርቃር እናበጅ ነበር።
እንግዲህ የቀን ውሏችንን በዚህ ዓይነት ሁኔታ ካለፍን በኋላ ሁልጊዜም በዙሪያችን የሚያንጃብቡትን ሳንቡሳና ፓስቲ ነጋዴዎች እንጐበኝ ነበር። ከዚያም በአካባቢያችን በናፍቆት የሚጠባበቁትን የሳይክል አከራዮችና የቪዲዮ ቤቶች የሸቀልናትን እናስረክብና ነገን በናፍቆት እንጠብቃለን።
በነገራችን ላይ ሁሌም የሚገርመኝ በቡሄ ወራት የነዚህ የብስክሌት አከራዮች፣ የሸንኮራ ነጋዴዎች ፣ የሳንቡሳ ሻጮች ቁጥር መጨመር ሲሆን፤ በሚያስደንቅ ሁኔታ በወቅቱ አብዛኛው ጨፋሪ ከዱላው አጠገብ ሳንቡሳ ወይም ሸንኮራ መያዝ የበዓሉ ሌላ መገለጫ ነበር።
Comments
Post a Comment