ዘረኛ ሰውና በቫይረስ የተጠቃ ሞባይል


ባልሳሳት የቃየል መስዋእት በሚለው የአማርኛ መጽሐፍ ላይ ይመስለኛል አንድ ጽሁፍ አንብቤ ነበር «ኤች.አይ./ኤድስን እና የዘረኝነት በሽታን አጥር አጥረህ ወታደር አቁመህ አትከላከላቸውም» ይላል። ምን አልባት አባባሉ እውነት ሊመስል ይችላል። ግን ሁለቱም ከተጠነቀቋቸው አይነኩም። ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ ተወልደሃል እንበል። ቤተሰቦችህ ከተለያየ የዘር ግንድ መጥተው አንተን ወለዱህ። እነሱ ቋንቋውን ያወሩታል። ሌላውን ባህል ግን ረስተውታል። አንተ ጋር ሲደርስ ደግሞ ቋንቋውም ባህሉም የለም። እና አንተ ምንን መሰረት አድርገህ ነው በዘር የምትጋጨው? ደሞ ዘርህ ለአንተ አፍሪካዊ አይደለምን? ከዛ ቀረብ ሲል ደግሞ ዘርህ ኢትዮጵያዊ አይደለምን? ዘር እኮ አዶልፍ ሂትለርን የጨካኞች ጨካኝ የአውሬዎች አውሬ አድርጎታል። ዘረኝነት ለርዋንዳ ምን አተረፈላት? ያንተ አማራ መሆን የአንተ ኦሮሞ ወይም ትግሬ አልያም ደቡብ መሆን ለኔ ምኔ ነው? ምንስ ትፈይድለኛለህ?አስተውላችሁ ከሆነ ብዙ ግዜ እዚህ በብሄሩ የሚኩራራ አንድ ኢትዮጵያዊ ከአገሩ ከወጣ በኋላ ያገኘውን አፍሪካዊ ሁሉ ማፍቀር ይጀምራል። የሀገሩንማ ልጅ ሲያገኝ አይደለም ብሄሩን ስሙን እንኳን ሳይጠይቅ ነው አብሮት ማውራት የሚጀምረው። ታዲያ ይህ ትውልድ ምን ነክቶታል? አራድነት ማለት እኮ ክብርን ጠብቆ እራስንም ሳያገኙ ሌላውንም ሳያኮስሱ መኖር ነው።
ስማኝማ ዘረኛ ሰውና በቫይረስ የተጠቃ ሞባይል አንድ ናቸው። ሁለቱም ቀዳዳ ካገኙ ዘው ማለት ይወዳሉ። ከዛስ? ከዛማ ፍዳህን ነው የሚያሳይህ። እመነኝ ሰውን ሁሉ ውደድ። ምንም አታጣም።

Comments

Popular Posts