የመዲ ቡና
የመዲ ቡና
ይህ ጽሁፍ ለግለሰቦች መብት ሲባል ስሞች ተቀይረዋል
የመዲ ቡና አራት ኪሎ ከሚገኙት የአርከበ ሱቅ ውስጥ ትገኛለች። ይቺ ቤት ጠዋትና ምሳ ሰአት ላይ የተለያየ ባህሪና ማንነት ያላቸውን ሰዎች ታስተናግዳለች። ከፍተኛ ከሚባሉት ባለስልጣናት አንስቶ እውቅና እስከተሰጣቸው እብዶች ይጎበኟታል። (በነገራችን ላይ እብድ ብለህ እንዳትጽፍ ተብዬ ነበር አውቄ ነው የተሳሳትኩት) ።
የመዲ ቡና ቤት የጋዜጠኛው፣ የፕሮፌሽናል ኳስ ተጫዋቹ፣ የባንክ ቤት ሰራተኛው፣ የህክምና ባለሙያው መስተናገጃ ናት። ሁሉም ሰብሰብ ብሎ ይመጣል...... በመጣበት እግሩ ለሰስ ብሎ ይሄዳል።
እናም የመዲ ቡና ለብዙ ሰዎች መገናኛ ከመሆንዋ የተነሳ የኔንም እይታ ስባዋለች ። እይታዬን ከሳቡት ትእይንቶች መካከል የመዲ እብዶች አንዱ ነው።
የመዲ ቋሚ እብዶች አራት ሲሆኑ ወንዴ የሚባለው እብድ አራዳ ነው። ሁሌም ሲመጣ ስጦታ ይዞላት ነው የሚመጣው። ጽጌሬዳ አበባ.... ቅጠላ ቅጠሎች... የመሳሰሉትን ያመጣላታል። መዲም ለዚህ እብድ ልዩ ፍቅር ስላላት እሱን ናፍቆት አይኖችዋ ሲነክራተቱ አይቸያታለሁ።
ወንዴ ሰው አይነካም። ደስ ያለው ቀን የመጽሃፍ ቅዱስ ቃል ሊጠቅስ ይችላል። ደስ ሲለው ደግሞ የሆነ ምንነቱ የማይታወቅ ቃልን ያነበንባል። ሲጃራ ያጨሳል :: ሰው ባለበት ቦታ ላይ ግን ላለማጨስ በጣም ነው የሚጠነቀቀው። እንደ ብዙ እብዶች በኮት ላይ ሹራብ በሹራቡ ላይ ቲሸርት ደርቦ ይለብሳልል። ጣቱ ላይ የብረት ቀለበት አይጠፋም። ምንነቱ የማያስታውቅ ኮተት በፌስታል ተሸክሞ ይዞራል።
አኬ ለላኛው የመዲ እብድ ነው። አራት ብሩን ይዞ ይመጣና ቡናውን እስኪጠጣ በትዝብት መልክ መዲን አፍጥጦ ያያታል። ቡናውን ከጠጣ በህዋላ ሩጫ በሚመስል ፍጥነት ይሄዳል።እነ ጆሲና እነ ስማቸወን የማላወቅው እብዶች የመዲ ለማዳ እብዶች ናቸው።
በመዲ ቡና ቤት ፖለቲከኛው.... ካድሬው.... ፖሊሱ ....ሲቪል ሰርቫንቱ.... ይታደማሉ። ቢሮ የጀመሩትንም "ኦፊስ ፖለቲክስ" እስዋ ጋር አወራርደው ይመለሳሉ። አጋጣሚ ሆኖ አለቃቸው ሲመጣ ደግሞ ድንጋይ እንደተወረወረበት ወፍ ግር ብለው ይጠፋሉ።
ትናንሾቹ የወረዳ ካድሬዎች የመዲ ቡና ቤት ቡና ቤት ታዳሚዎች ናቸው:: ። ወሬያቸው ሁሉ ያስጠላል። ቀልድ ወይም ቁምነገር ማውራት አይችሉም። መልካቸው ስለሚመሳሰልብኝ አንዳንዴ ማንን እያየሁ ወይም እየሰማሁ እንዳለ አላውቅም። ወንዱም ሴቱም አንድ ነው መልካቸው። በነሱ ወሬ የኢትዮጵያ ዛቢያ በነሱ ጣት ላይ ናት ያለው። የነሱ ስብሰባ የአዲሲቱ ኢትዮጵያ ጀርባ አጥንት የሆነ ስለሚመስላቸው ሲያወሩ.... ሲያወሩ.... አይሰለቻቸውም።
መዲ ጋር የምታደሙት "የሰው መብት ጠባቂዎችም" ሌላው እይታዬን የሳቡ ግለሰቦች ናቸው:: አንዳንዴ ወራዳ የሆነ ቃል ሲጠቀሙ አስተውያለሁ። ህዝብ ሰላም እንዲያስከበር ሃላፊነት የሰጠው ፖሊስ ሴት በመላከፉ የተሰማውን ደስታ በትምክህት ሲናገርም ሰምቼዋለሁ።
Comments
Post a Comment