አምባ ገነኖቹ መምህሮቼ




አምባ ገነኖቹ መምህሮቼ
በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተጻፈ ነው
በልዑልሰገድ ወርቁ
ገና የአንደኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ነው ትምህርትና አስተማሪን የጠላሁት። የቄስ ትምህርቴን ያቋረጥኩት የኤኒታ ዱላ ጭንቅላቴን ሲቀውረኝ ያስተዋለች እናቴ ልጄን አናቱን እየደበደቡ ችግር እንዳያደርሱበት በሚል ፍራቻ በቀጥታ ወደ አንደኛ ክፍል ነው ያስገባችኝ።
የቄስ ትምህርቴ "" "" ን እና "አቡጊዳን" ስላልዘለለ ምንም ትዝታ የለኝም።።ትዝ የሚሉኝ ነገሮች ቢኖሩ የአኒታ እንቅልፍ፣ በሽሮፕ ጠርሙስ ይዘናት የምንሄዳት ውሃ፣ ከየቤታችን የምንወስዳት ዱካእና የዬኒታ የማያቋርጥ የበአላት ቀን ብዛት ናቸው።

ልክ አንደኛ ክፍል ስገባ ሁሉ ነገር ለኔ ግራ የሚያጋባ ነበር። ሰፊ ክፍል ውስጥ የታጨቁ ብዙ ቁጫጮች......በአንድ ዴስክ ላይ እየተገፋፉ የተቀመጡ አራት ፈልፈላዎች........ያንን በሚያክል አዳራሽ ውስጥ የበራች አንዲት 60 ሻማ አንፖል....! በቃ ሁሉ ነገር ድንብርብር የሚያደርግ ነበር።

የመጀመሪያዋ አስተማሪዬ ወደ ክላስ ገባች። ያሁሉ ጩኸት እረጭ አለ። "እያንዳንድሽ ከዚህ ሰአት ጀምሮ ብትጮሂ በዚህ ዳስተር ነው ግንባርሽን የምልሽ...!!" :: ልቤ በአፌ ልትወጣ መፍጨርጨር ጀመረች። ይቺ የአማርኛ መምህሬ ፊትዋ ቀይ ቢሆንም የሆነ ጥቁር ጭራቅ መስላ ታየችኝ። ስሟ ሃረገወይን ቢሆንም ለኔ ግን ሀረግ እሬሳ ሆኖ ነው የገባኝ።

በስንተኛው ቀን እስዋ እያስተማረች ሽንቴ ወጠረኝ። ምን ውስጥ ልግባ....:: ማንም ተማሪ ደፍሮ "ቲቸር ሽንቴ ወጠረኝ" ሲላት ሰምቼ አላውቅም። ምን ይዋጠኝ....? ልብሴ ላይ አለቀው ነገር እናቴ በንጽህና ጉዳይ እንዳልደራደር አድርጋ ነው ያሳደገችኝ።

ሽንቴ አሁንም ፋታ አልሰጠኝም...... በቃ..... እዛው ቁጭ እንዳልኩ መሽናት አማራጭ መሆኑን ውስጤ ሹክ አለኝ። ሸናሁት:: ግን አለመታደል ሆኖ ሽንቴ ከፊት የተቀመጠው ብላቴናን አርሶት ስለነበር ወዲያውኑ "ቲቸር ሽንቱን ሸናብኝ..!” አላት። ምን ውስጥ ልግባ....? በቃ... ስትፈለግ በዳስተሯ ትፈንክተኝ ሁልተኛ ግን ወደዚህ ትምህርት ቤት አልመጣም ስል አሰብኩ። የሚገርመው ግን በቃ ያቺ እርጉም አስተማሪ የዚያች ቀን መልካም ሆነችልኝ። ሰው ልብስ ላይ የጀመርኩትን ሽንት ወጥቼ እንድጨርስ ፈቀደችልኝ።

ይህ በመጀመሪያ ደረጃ ያስተዋልኩት የመምህራን ጭካኔና ፍራቻ በአማርኛ ቲቸሬ ብቻ አልነበረም የሚስተዋለው። የእጅ ስራ መምህራችን ነፍሱን ይማረውና በጣም ጨካኝ ነበር። ሁሉንም አይነት የጭካኔ ቅጣቶች ያውቅባቸዋል። በቃሪያ ጥፊ ተማትቶ ሰውን ነስር በነስር ከማድረግ እስከ ጣትን በእስክሪቢቶ ቀፎ እስከመቀርጠፍ ይደርሳል። ሲያምረውም በቦክስ ሊማታ ይችላል። የነቲቸር ያቺ ጎማቸውም የዲያቢሎስ ጭፍራ መሆናቸውን ታስታውሰኛለች።

ይህ የመምህራን አውሬ ባህሪ ከፍተኛ ትምህርት ተቋምም አስተውዬዋለሁ። ሁልጊዜ እራሳቸውን አዋቂ አድርገው የሚያዩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎቼ ናቸው። እንገሊዘኛ መቀባጠር የእውቀተት ሁሉ የእውቀት ሁሉ እውቀት አድርገው ነው የሚቆጥሩት። ቢቻላቸው አማርኛንም በእንግሊዘኛ ከማስተማር አይቦዝኑም። ለኔ እነሱ እንጊሊዘኛ ምኔ ነው? የኢትዮጵያን ታሪክ በእንግሊዘኛ ማስተማር ይሻላል ወይስ በአማርኛ? ለኢትዮጵያ ታሪክ የሚቀርበው አማርኛ ነው እንጊሊዘኛ? ሲቀጥል ደግሞ ሁሌ እነሱ እንደፈሱት እኔም መፍሳት አለብኝ? Where is my golden word? ከሚል ደነዝ ሌክቸረር ጀምሮ እርሱ እራሱ የማይመልሰውን ፈተና እስከሚፈትነው ድረስ ያሉት የስድስት ኪሎ ሌክቸረሮች ጥሩ ማሳያዎች ይመስሉኛል። ፊቱን ስላኮፈሰ አዋቂ የሚመስለውም ሌላው ትዝታዬ ነው።
አንዳንዴ ሳስበው የሃገሬ ፖለቲካ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ይመስለኛል። መሪዎች አምባ ገነንን ቢሆኑ በነሱ ይፈረዳል? በተ አምር።ባለስልጣናት ለህዝቡ የማይቆረቆሩ ቢሆኑ ይፈረድባቸዋል? በጭራሽ..!! አምባገነን መምህር ያስተማረው ፖለቲከኛ ጨካኝ ባይሆን ይገርመኝ ነበር። ብዙዎቹ ማለት በሚያስደፈር ሁኔታ የሃገሬ ባለስልጣናቶች ፈገግ ብሎ ከህዝቡ ጋር ከመኖር ይልቅ እራሳቸውን ቆልለው ከህዝብ ተለይተው ነው የሚኖሩት። ምክንያቱም እራሱን የቆለለ መምህር ካስተማረው ትውልድ ምን ይጠበቃል? ሳያውቅ እንደሚያውቅ "አክት" በሚያደርግ መምህር የተከተበ ተማሪ መጨረሻው ያው እንደ መምህሩ ነው።

Comments

Popular Posts